Asset Publisher

ሦስተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ ሙሌት በሐምሌ ወር እንደሚጀመር ታወቀ
ሦስተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ ሙሌት በሐምሌ ወር እንደሚጀመር ታወቀ
የሁለተኛው ተርባይን ፍተሻ ተጀምሯል
ለመጀመሪያ ጊዜ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ሦስት ወራት ያለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት፣ ከመጪው ሐምሌ ወር አንስቶ መከናወን እንደሚጀምር ታወቀ፡፡
ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ ወደ ግድቡ የሚፈሰው የውኃ መጠን ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ከፍ እያለ ከሄደ በኋላ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውኃ በመያዝ፣ በሐምሌ ወር ሙሌቱ እንደሚጀመር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ወደ ግድቡ እንዲገባ የሚጠበቀውን የውኃ መጠን ለመያዝ የግድቡን ቁመት የመጨመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የውኃ ሙሌቱ ሲጀመር የግድቡ ቁመት በሚፈለገው መጠን እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡
ከክረምቱ መግባት በኋላ ባሉት ወራት የሚኖረው የውኃ መጠን የሚለያይና እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ከፍተኛው የውኃ መጠን የሚታየው በነሐሴ ወር ነው ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከሐምሌ ጀምሮ የሚፈለገው የውኃ መጠን ተይዞ፣ በነሐሴ ወር ውኃው በግድቡ ላይ ይፈሳል ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በሰኔ ወር መጨረሻ ሲጀመር በነሐሴ ወር አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ በዓመቱ በነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ፍሰት የተነሳ መጠናቀቁ የተበሰረው ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የ2014 ዓ.ም. የክረምት ወር ትንበያ፣ አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር አሳይቷል፡፡
በዚህ ዓመት ምን ያህል የውኃ መጠን ለመያዝ እንደታቀደ ባይገለጽም፣ መንግሥት ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ምን ያህል ውኃ ለመያዝ ማቀዱን አስታውቆ ነበር፡፡ ሙሌቱ በተጀመረበት 2012 ዓ.ም. የግድቡ ቁመት 565 ሜትር ሆኖ 4.9 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙ መገለጽ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት የግድቡን ቁመት 595 ሜትር በማድረስ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ለመሙላት ታቅዶ ነበር፡፡ ይህም ሙሌቱ በተጀመረ በሁለተኛው ዓመት ግድቡ የሚይዘውን የውኃ መጠን 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚያደርስ ነው፡፡
በሦስተኛው ዓመት ላይ የግድቡን ቁመት 608 ሜትር ከፍታ ላይ በማድረስ 10.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመሙላት፣ አጠቃላዩን የውኃ መጠን 28.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማድረስ ውጥን እንዳለ ዕቅዱ ያመላክታል፡፡ የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ውኃ የመያዝ አቅም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
ባለፈው ዓመት የተደረገው የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ሲበሰር የውኃው መጠን ሁለት ተርባይኖችን ማንቀሳቀስ የሚችል እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡
የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር የፍተሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ወር ከግማሽ እስከ ሁለት ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የፍተሻ ሥራዎች አጠናቆ ኃይል ማመንጨት ማስጀመር እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
ኃይል ማመንጨት የጀመረው አንዱ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተነግሮ የነበረ ሲሆን፣ ሁለተኛውም ተርባይን ተመሳሳይ የማመንጨት አቅም እንዳለው ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹ማመንጨት የሚችለው [ኃይል] እንደ ውኃው ከፍታ ይለያያል፣ አሁን ባለው የውኃ ከፍታ መጠን ማመንጨት የሚችለውን ያህል ያመነጫል፤›› ብለዋል፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ