“ግብጾች ማጥቃት የሚፈልጉት ግድቡን ሳይሆን ስነ ልቦናችንን ነው”- ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በህዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ባለሙያ ቡድን አባል - መነሻ - am

Nested Portlets

Asset Publisher

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት 11 ወራት ከ984 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ Fri, 17 Jun 2022

ታንዛኒያ ሕዳሴ ግድቡ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገለጸች Wed, 8 Jun 2022

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የዋንጫ አቀባበል ሥነ-ሥርዓት በአዳማ ተካሄደ፡፡ Wed, 8 Jun 2022

Statistics

× አድራሻቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ኢትዮጵያ.
× ግንባታዉ የተጀመረበት ጊዜ :2011 እ.ኤ.አ.
×ስፋት፡1,874 ስየር ኪሎ ሜትር
× የመያዝ አቅም: 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር

Asset Publisher

“ግብጾች ማጥቃት የሚፈልጉት ግድቡን ሳይሆን ስነ ልቦናችንን ነው”- ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በህዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ባለሙያ ቡድን አባል

ግብጾች ማጥቃት የሚፈልጉት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ሳይሆን ስነ ልቦናችንን መሆኑን በህዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ባለሙያ ቡድን አባል ዶክተር በለጠ ብርሃኑ አስታወቁ። ግብጾች የአባይን ጉዳይ ካላራገቡ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ እንረሳለን የሚል ስጋት እንዳላቸውም አመለከቱ።

ዶክተር በለጠ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ የግብጾች ፍላጎት በኛ ስነ ልቦና ላይ ጫና በመፍጠር ግራ እንድንጋባ ማድረግ ነው። ለዚህም ነው የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ስነ ልቦናችን ላይ ጫና ለመፍጠር የሚጥሩት።

ግብጻውያኑ በኛ ስነልቦና ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጓቸው ጥረቶች እንዳሰቡት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን የእንችላለን መንፈስ እንዲያሳድጉ አድርጓቸዋል ያሉት ዶክተር በለጠ፤ እኛ እንዲህ ነን ለማለት ብዙ ርቀት መሄድ እንቸገራለን። እነሱ ደግሞ በዚህ ለመጠቀም እድል አግኝተዋል ብለዋል።

ግብጾች በየወቅቱ የሚያሳዩት የአቋም መቀያየር ግራ መጋባታቸውን የሚያሳይ ነው። ሁሌም የግብጽ ችግር በውስጣቸው ያለውን ውጥረት ትተው ወደዓለም አቀፍ ጉዳይ ሲያተኩሩ የሚመጣባቸው ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሌም አጀንዳ አድርገው ማቅረብ የሚችሉት የአባይን ጉዳይ ነው። የአባይን ጉዳይ ካላራገቡ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ እንረሳለን የሚል ስጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

አሁን የፍልስጤምና የእስራኤል ጉዳይ ውስጥ መግባት በመፈለጋቸው የናይልን ጉዳይ በትንሹም ቢሆን ተወት አድርገውት እንደነበር ያመለከቱት ዶክተር በለጠ፤ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለፓርላማው የሁለተኛው ዙር ውሃ ቢሞላም ብዙ ጉዳት አይኖረውም ሲሉ የገለጹት ከዚሁ የተነሳ መሆኑን አመልክተዋል።

ቀደም ሲል ግብጽ ለህዝቧ ታቀርብ የነበረው ትርክት የናይል ውሃ ባለቤት የግብጽ ህዝብ እንደሆነ ነው። ፖለቲካቸውም የሚመሰረተው በዚህ ጉዳይ ነው። በየጊዜው የሚመጡ መሪዎቻቸው የመጀመሪያቸው ነገር የናይል ውሃን መብት ማስከበር መሆኑን መናገር ነው አልሲሲም የናይልን የውሀ ባለቤትነት አስከብራለሁ በሚል ወደ ስልጣን መምጣታቸውን አመልክተዋል። ከዚህም የተነሳም ውስጣዊና ውጫዊ ግራ መጋባት እንደሚያጠቃቸው ጠቁመዋል።

ይህንን ይዘው ጉዳዩን ወደእኛ በማምጣት እኛ በነገሮች ሁሉ እንድንጨነቅ ይፈልጋሉ ያሉት ዶክተር በለጠ፤ በእርግጥ ግብጾች መቼም ቢሆን አደጋ አያደርሱብንም፤ ወደጦርነትም መግባት አይፈልጉም ብለዋል።

ግብጽ በየወቅቱ የምታሳየው የአቋም መቀያየር የሚያሳድረው ተጽዕኖ የዚያን ያህል ነው። በግድቡ ላይ ብዙ የተለየ ተጽዕኖ አያመጣም። በውሃ ግድብ ላይ እንደሚሰራ አንድ ባለሙያ ይህን የግብጽን መቀያየር እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊታይ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

የግብጽ የአቋም መቀያየር የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለአባይ ውሃ ያለው ትኩረትና ግንዛቤ ከፍ እንዲል አድርጓል። በህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ ተንጠልጥለን የምንቀር ሳንሆን ሌላም ግድብ የመስራት ተነሳሽነትን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

እኛ በመርሆዎቹ ስምምነት ላይ የተስማማነው በውሃ መልቀቅና መሙላት ስርዓት ላይ እንግባባለን በሚል ነው። እነሱ ግን የሚፈልጉት በዚህ ግድብ አማካይነት ኢትዮጵያ ወደፊት የምታለማውን ነገር መቆጣጠር ነው። ከዚህም የተነሳ በእያንዳንዱ ድርድርና ውይይት ቦኋላ አሳሪ ህግ እንዲቀመጥላቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ለዚህም ነው ገና መቶ ግድብ እንገድባለን የሚለው ሐሳብ ያስበረገጋቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ እንዳትጠቀም እና ታስራ እንድትቀመጥ ነው የሚፈልጉት። እኛ ደግሞ መበርታትም ያለብን እዚህ ላይ ነው። ኢትዮጵያውያን በጠነከርን ቁጥር ግብጾች እየተረበሹ ይመጣሉ ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወሳኝ ማዕከል መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር በለጠ፤ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ካሉት አገሮች መካከል ትልቅ አቅም ያላት ናት ኢትዮጵያ ላይ ጫና መደረግ ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ ስጋት መፍጠሩ እንደማይቀር አሳስበዋል።

ሌላው ቢቀር ቀጣናው ላይ ችግር ቢከሰትና ሰዎች ስደተኛ ቢሆኑ ይህ ሁሉ የት ነው የሚሰደደው። የሚሰደደው በጎረቤት አገሮች እንደመሆኑ ለእነሱ ይህም ስጋት ሊሆን ይችላል፤ በቀጣናውም ስጋት ይፈጠራል። ይህ በመሆኑ በቀጣናው ያሉ አገራት ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና አግባብ አይደለም ብለው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሊጠይቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ግብጽ ህዝቤ በቁጥር ብዙ ነው፤ ቢራብ ወይም በደህንነቱ ላይ አደጋ ቢጋረጥበት ተሰዶ የሚመጣው በአቅራቢያዬ ባሉ አውሮፓ አገራት ነው ትላለች። ወደ እናንተ ቢሰደድ ደግሞ የሚጎዳው የእናንተኑ ኢኮኖሚ ነው። ጠብታ ውሃ ቢቋረጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ከስራ ውጭ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁሉም ወደ አውሮፓ አገር ይሰደዳል የሚል ስትራቴጂ እንደምትጠቀም አስታውቀዋል።

ልክ እንደእሷ ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ጫና ለሱዳንም፣ ለሱማሊያም፣ ለጅቡቲም ሆነ ለኬንያ፣ ለኤርትራና ለደቡብ ሱዳንም ጭምር ጫና ነው። ስለዚህ እነዚህ አገራት በአንድነት ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው ብለዋል።

አብዛኛውን ጊዜ የእኛ ዲፕሎማሲ የተንጠለጠለው በጊዜያዊ ስሜት ላይ ነው። አጀንዳው ሲግል ሁላችንም እንግላለን። ሲቀዘቅዝ ደግሞ እንቀዘቅዛለን ያሉት ዶክተር በለጠ፤ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ አጀንዳ የምንሰጣቸው እኛ ሳንሆን እነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ከዚህ አንጻር ዲፕሎማሲያች አጀንዳ ሰጪ መሆን እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

ምንጭ፡-አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2013 .

Nested Portlets

Asset Publisher

— 5 Items per Page
Showing 1 - 5 of 16 results.