እምቦጭ ፤ ከጣና እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ - መነሻ - am

Nested Portlets

Asset Publisher

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት 11 ወራት ከ984 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ Fri, 17 Jun 2022

ታንዛኒያ ሕዳሴ ግድቡ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገለጸች Wed, 8 Jun 2022

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የዋንጫ አቀባበል ሥነ-ሥርዓት በአዳማ ተካሄደ፡፡ Wed, 8 Jun 2022

Statistics

× አድራሻቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ኢትዮጵያ.
× ግንባታዉ የተጀመረበት ጊዜ :2011 እ.ኤ.አ.
×ስፋት፡1,874 ስየር ኪሎ ሜትር
× የመያዝ አቅም: 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር

Asset Publisher

እምቦጭ ፤ ከጣና እስከ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አሜሪካ ሀገራት የታየው እንቦጭ አረም ዛሬ ላይ  በኒውዚላንድ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ካምቦዲያ፣ ሉዊዚያና ፣ አሜሪካ፣ ሕንድ፣ እና በቪክቶሪያ ሀይቅ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ማላዊና ግብጽ ከባድ የራስ ምታት ሆኗል።
‹‹ሀርትቢስ ፑርት›› በደቡብ አፍሪካ፤ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ለመስኖ አገልግሎት እንዲውል የተገነባ ግድብ ነው፡፡ በተጨማሪ የውሀ ላይ ስፖርት የሚዘወተርበት የመዝናኛ ሥፍራም ሆኖ ለቱሪዝም አገልግሎት ሲውል ቆይቷል፡፡ በዚህ ግድብ ላይ በ1970ዎቹ መታየት የጀመረው እምቦጭ አረም ዛሬ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የግድቡን የውሀ አካል በመሸፈኑ የውሀ ጥራትና መጠን ከመቀነሱም በላይ ምንም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉ እንቅፋት ፈጥሯል ፤በቱሪስት ፍሰት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡
ይህን በምሳሌነት ጠቀስኩ እንጂ ዋናው ጉዳዬ እምቦጭ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በጣና ሀይቅ ላይ እየተስፋፋ የመምጣቱ ነገር ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ በጊዜ ካልታሰበበት ነገ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን መጠቆም ነው፡፡
የእምቦጭ አረም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በ1956 ዓ.ም አባ ሣሙዔል ግድብ ላይ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።ነገር ግን በወቅቱ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ይህ መጤ አረም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በታላላቅ ሀይቆቻችንና የሀይል ማመንጫ ግድቦቻችን ሳይቀር መታየቱ ስጋት ፈጥሯል፡፡
በተለይም ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በታላቁ የጣና ሀይቅ ላይ አረሙ በፍጥነት እየተስፋፋ ከመሆኑም በላይ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና 35 ቀበሌዎች በሚገኙ የውሀ አካላትን ማዳረሱ እየተነገረ ነው።በአሁኑ ወቅት በጣና ሀይቅ ላይ ያለው የእምቦጭ አረም መጠን 900 ሄክታር አካባቢን የሸፈነ መሆኑንም አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እምቦጭ በጣም በፍጥነትና በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችል አረም በመሆኑ በየሁለት ሳምንቱ መጠኑ በእጥፍ እየጨመረ የሚሄድ በውሃ ላይ የሚበቅል ወራሪ አረም ነው፡፡የውሃ ጥራትና መጠንን መቀነስ፤ የብዝሀ ህይወትን ማዛባት/የዓሳ እና ሌሎች በውሀ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረቶችን ማጥፋት/ ፣በውሃ ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን መቀነስ ፣መንገድ፤ህንጻና ግድብ የመሳሰሉትን መሰረተ ልማቶች  ማበላሸት  አረሙ ከሚያስከትላችው ጉዳቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንዲሁም የአንድን የውሃ አካል ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ በማወክ አካባቢው በጎርፍ እንዲጠቃ በማድረግ የእርሻ መሬቶች፤እንስሳትንና ሌሎች ንብረቶችን እንዲወድሙ ያደርጋል፡፡ የአካባቢን ውበት ያበላሻል ፤ የውሀ ላይ ትራንስፖርትን ያስተጓጉላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በሰው ልጅ ላይ  የጤና ችግር ያስከትላል፡፡
እምቦጭ አረም በብዝሃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ ነው፡፡ በጣና ሀይቅና በአጠቃላይ በጣና ተፋሰስ ዙሪያ የእርሻ መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ፍሳሾች አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑም  ይነገራል፡፡
የዓባይ መነሻ ነው የሚባለው ጣና ሀይቅ በመጤው የእንቦጭ አረም እየተጠቃ በመምጣቱ ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንቦጭ በቀላሉ የመስፋፋት ባህሪ ያለው በመሆኑ አስፈላጊው ርብርብ ተደርጎ ማጥፋት ካልተቻለ ከጣና አልፎ በህዳሴ ግድብ ላይ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል በመኖሩ ነው፡፡
የህዳሴ ግድብ ሲገነባ ከ50 እስከ 100 ዓመት ያገለግላል በሚል እሳቤ ነው፡፡ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ ወደ ሱዳንና ግብፅ ይገባ የነበረውን ከ1ቢሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ደለል ይዞ ያስቀራል፡፡ ፡፡ይህን ያህል መጠን ያለው ደለል እየገባ በግድቡ መከማቸቱ የእምቦጭ አረም ወደ ግድቡ የሚገባ ከሆነ በቀላሉ ለመስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን በግድቡ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖም ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ደለል እና እምቦጭን በጊዜው መከላከል ካልቻልን የግድቡ የአገልግሎት ዕድሜ ሊያጥር እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ይሁንና ከአርሶ አደሩ የመኖሪያ እና የእርሻ ማሳ ጀምሮ የአባይ ተፋሰስን ግምት ውስጥ ያስገባ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ መስራት ከተቻለ የግድቡን የአገልግሎት ዘመን ከማርዘም በላይ የእምቦጭ አረም በውሀ አካላት ላይ እንዳይስፋፋ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የተሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
ቢቻል ደግሞ የአባይ ተፋሰስ ልማትን ሱዳን እና ግብጽን በማሳተፍ በጋራ ቢሰራ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም እነዚሁ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በሀገራችን በየዓመቱ 92,000 ሄክታር የደን መሬት ይራቆታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው የአፈር መሸርሸር ባለፉት ዓሥርት ዓመታት በወንዞቻችንና ሀይቆቻችን ላይ በደለል የመሞላት እና በዚህም ምክንያት የውሀ መጠን መቀነስና መሸሽ እንዲከሰት አድርጓል፡፡ ለአብነት ፡- ሀረማያ፡ አብጃታ ፣ሐሸንጌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እምቦጭ ከጣና ሀይቅ አልፎ የግድቡም ስጋት ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም በማለት በርካቶች ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ም/ቤት ጉባኤዎች ላይ የእምቦጭ ጉዳይ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችም፤ መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ባለሀብቶች እምቦጭን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ እንዲሳተፉ በተለይም አረሙ በዘላቂነት የሚጠፋበትን ሳይንሳዊ አሰራር መከተል እንደሚገባ አቅጣጫ የሰጡበት ሁኔታ ነበር፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ወጣቶች፣የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የተለያዩ አካላት የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት በእጅ ከመንቀል አንስቶ ማሽነሪዎችን በመጠቀም የተለያዩ ጥረቶች አድርገዋል፡፡ነገር ግን እምቦጭ በእጅ ተነቅሎ ብቻ የሚጠፋ አሊያም በጥቂት ማሽኖች ርብርብ ሊወገድ የሚችል አልሆነም፡፡ ይልቁንም አረሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዞታውን እያሠፋ የሄደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጥረቱ ውጤታማ አለመሆኑን የተገነዘበው መንግስት በቅርቡ አረሙን ለማጥፋት የሚያስችለውን ስትራቴጂ አዘጋጅቶ የሚመለከታቸውን አካላት ያወያየ ሲሆን ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ በእምቦጭ ላይ እንደሚዘምትም አስታውቋል፡፡
ስትራቴጂክ ዕቅዱ አረሙን ማስወገድ፣ በዘላቂነት የውኃና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች መስራትና ነፃ የሀይቅ ዳርቻ መፍጠር እንዲሁም በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ጣናን ከእምቦጭ ለማጽዳት ተዘጋጀ የተባለው ይህ ስትራቴጂ ውጤታማ እንዲሆን ችግሩ ያሳስበናል የሚሉ አካላትም ሆነ ህብረተሰቡ እንቦጭን ለማጥፋት በየግላቸው ከመንቀሳቀስ ይልቅ በተጠና ሁኔታ በጋራ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።
ከልማዳዊው አሰራር ወጥተን በስትራቴጂ የተደገፈና የተቀናጀ እምቦጭን የመከላከልና  የማስወገድ ስራ ማከናወን ስንችል ብቻ ነው ግዙፉን የጣና ሀይቅም ሆነ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን  ከጥፋት መታደግ የምንችለው፡፡
ምንጭ፡- የታላቁ ህዳሴ/ግ/ግ/ህ/ተ/አ/ብ/ም/ጽ/ቤት

 

Nested Portlets

Asset Publisher

— 5 Items per Page
Showing 1 - 5 of 16 results.