Asset Publisher

የአባይ ትውልዶች ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)

በዘመናት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ብዙ ትውልዶች መተው ሄደዋል። ወደ ፊትም አዳዲስ ትውልዶች ይፈጠራሉ። ይሄ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። በዚህ የትውልድ ሽግግር ውስጥ ግን የሚፈጠሩ ሀገራዊ መልኮች አሉ። ሁሉም ሀገር የራሱ ትውልዳዊ አሻራ አለው። ሁሉም የዓለም ህዝብ የራሱ ትላንትናዊ የታሪክ ዳራ አለው። በኢትዮጵያ ታሪክም በርካታ ጉራማይሌ ትውልዶች የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ አልፈዋል። በዚህ የታሪክ መመላለስ ውስጥ ግን ስመ ገናና ግዩናዊ ትውልድ ተፈጥሯል።

ዘመን በዘመን ተተክቶ እንሆ የአባይ ትውልዶች ላይ ደረሰ። እርሱም እኛ ነን። እርሱም ባለታሪክ ትውልድ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ የሚጀምረው ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ነው እላለሁ። በዚህ ህይወታዊ መመላለስ ውስጥ ለሌሎች የሰጠውና ከሌሎች የተቀበለው ሀገራዊና ማህበራዊ እሴት ተመዝኖና ተለክቶ ሊያስመሰግነውም ሆነ ሊያስወቅሰው ይችላል። መኖራችን ትርጉም የሚኖረው ላለንበት ዘመን በከፈልንው የላቀ ዋጋ ልክ ነው እያልኩ ነው። በኖርንበት ጊዜና ዘመን ላይ ለሰው ልጅ ጠቃሚና ዋጋ ያለውን ተግባር ሠርተን ስናልፍ ያኔ የእውነት ኖረናል ማለት ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት ለሀገር በከፈለው ታላቅ ጀብድ የዚህኛውን ዘመን ትውልድ ባለታሪክ ትውልድ ስል ጠርቼዋለሁ።

አባቶቻችን በዘመናቸው ታላቅ ነገር ሠርተው አልፈዋል። ፊተኞቻችን በኖሩበት ዘመን ላይ ታላቅ ሀገርና ታላቅ ህዝብ አስረክበውናል። እኛ ደግሞ ከነሱ በወረስንው የአልሸነፍባይነት ውርስ አባይን የደፈረ ትውልድ ተብለን ስማችንን በታሪክ ድርሳን ላይ ከትበናል። አሁን የእኛ ጊዜ ነው። ለሀገራችን መልካሙን ለማድረግ በብርሃን ውስጥ ነን። በዘመናችን ላይ ጀግና ሆነን ለመቆም ጊዜው አሁን ነው። በዚህ ዘመን ላይ ያለ ምክንያት አልተገኘንም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሰነቀችው ብርሃናማ ነገ እኛ መሪዎቿ ነን። እንደሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ የአባይ የትውልድ ሀገር ናት። ሆኖም ግን በአባይ ላይ የበላይነትን ተነጥቀን ለበርካታ ዘመናት ኖረናል። ተወልዶ ባደገበት ሀገርና ህዝብ ውስጥ እየኖረ ለሌሎች የጸጋና የበረከት ምንጭ ሆኖ ሰንብቷል። በደጃችን ሲሄድ እያየንው በሙገሳና በሽለላ ሸኝተንዋል። አፈራችንንና ለም መሬታችንን እየጠራረገ ወደ ጎረቤት ሀገር ይዞ ሲሄድ በቁጭት ቆመን አይተንዋል።

በአባይ ላይ ያላዘነ ቂም ያላዘ ትውልድ የለም። አባይ ተገድቦ ለሀገራችን ተስፋና ብልጽግና ሲሆን ለማየት ያልጓጓ አልነበረም። አባይ ተገድቦ ብርሃን ሲሰጥ ለማየት ያልናፈቀ አልነበረም። ያኛው ትውልድ አባይ ተገድቦ ለማየት የናፈቀውን ያክል ምንም ነገር ናፍቆ አያውቅም እላለሁ። አባይ የአባቶቻችን አደራ ነው። አባይ የዚያኛው ትውልድ የቁጭትና የጸጸት ውርስ ነው። አባይ የብዙ ኢትዮጵያዊያን የጋራ መልክ፣ የጋራ ወዝ ነው። አባይ ለእኛ ወንዝ ብቻ አይደለም። ታሪካችንም ጭምር ነው። ከትላንታችን ጋር የተሸመነ ከዛሬአችንም ጋር የተቆራኘ ሀበሻዊ እንባና ሳቃችን ነው። በዚህ ርስታችን ላይ ለመጣ ደግሞ ምህረት የለንም። እንደ ዓድዋ አንድ ሆነን የቆምንበት፣ በብዙ ልዩነት ውስጥ ያስተሳሰረን የአንድነታችን ዋልታና ማገር ነው። በዚህ እውነት ላይ ለመጣ ማንኛውም ኃይል ይቅርታ የለንም። እየተራብን የገነባንው፣ እየተጠማን የሠራነው በብዙ ማጣት ውስጥ ሆነን ያቆምንም የመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የመታሰቢያ ሀውልት ነው። በዚህ ሀቃችን ላይ ለመጣ ቋያ እሳት ነው ክንዳችን።

አባይ እኔና እናተን ነው። አባይ ከዘፍጥረት ጀምሮ በደጃችን የሚፈስ፣ ቅድመ ዓለም የነበረ ድህረ አለምም የሚኖር አምላካዊ ስጦታችን ነው። ድህነት ዘር አይውጣለትና ይሄን ሁሉ ነገራችን የሆነውን አባይን ገድበን ለልማት እንዳንጠቀመው ሆነን ኖረናል። ማጣት የት አባቱንና እጅ አጥሮን የአባይን የትንሳኤ ብርሃን ሳናይ ብዙ ዘመን አሳልፈና። እንሆ ዛሬ በእኛ ሊገደብ አባይና ታሪኩ ተንከባሎ እኛ ትውልድ ላይ ደረሰ። ይሄ ትውልድ ፍም እሳት ነው። ይሄ ትውልድ አባይን የደፈረ ትንታግ ኃይል ነው። ይሄ ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያሻግር መለኮታዊ ኃይል ይመስለኛል። ይሄ ትውልድ የአባቶቹን አደራ ለመፈጸም ሲል ከሌለው ላይ ቀንሶ፣ ከሚበላው ላይ ገምሶ ለአባይ ትንሳኤ ሰጥቷል። ይሄ ትውልድ የነገን ብርሃን ሽቶ እውቀቱን ገንዘቡን ጉልበቱን ለአባይ ጀባ ብሏል።

ከሌለ ላይ እንደመስጠት እውነት የለም። ከሌለ ላይ እንደ ማካፈል ጽኑ የሀገር ፍቅር የለም። ይሄ ትውልድ አባይን ገድቦ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት ላሳየው ቁርጠኝነት ላመሰግነው እወዳለሁ። ይሄ ትውልድ በአባይ ዙሪያ የተነሱበትን የውጭ ጠላቶች ተቋቁሞ ኢትዮጵያን ለማሻገር እያደረገ ያለውን የአብሮነት ትግል ሳላደንቅ አላልፍም። በዚህ ትውልድ ውስጥ ሀሰት የለም። የኢትዮጵያ የዘመናት ድህነትና ኋላ ቀርነት በዚህ ትውልድ የተባበረ ክንድ የሚያበቃ ይመስለኛል። ይህ ትውልድ የኢትዮጵያውያን አንድ እውነት ነው። በዚህ ትውልድ ውስጥ ልማት እንጂ ቂምና በቀል የለም። በዚህ ትውልድ ውስጥ አንድነትና ህበረት እንጂ መለያየት ዋጋ አይኖረውም። ምክንያቱም የአባቶቹን አደራ ከዳር ለማድረስ የሚሮጥ ግዮናዊ ትውልድ ነውና ነው።

እናተ የአባይ ትውልዶች እያሳያችሁት ላለው ሀገራዊ ቀናነት ትውልድ ያመስግናችኋል። በዛሬና በነገ መካከል ያለ ታሪካዊ የትስስር ገመድ ናችሁና። አባይን ጨርሰን የምንፈነድቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአባይ መሳካት የበኩሉን በማድረግ ከዚህ ትውልድ መካከል ስሙን በወርቅ ቀለም መጻፍ አለበት። ለሀገራችን መልካም ለመሥራት ምርጡ ጊዜ ላይ ነን። ሀገራችንን እንወዳለን የምንል ከወሬ ባለፈ በተግባተር የምንፈተንበት የደስታና የጭንቅ ወቅት ላይ ነን። አባይ የእኔና የእናተ የህብረት ውጤት ነው። ተያይዘንና ተደጋግፈን እዚህ አድርሰንዋል አሁንም በአንድነት ፍጻሜውን እናይ ዘንድ አንድ ሆነን መቆም ግድ ይለናል። በአለንበት ዘመን ላይ ለአባቶቻችን ክብርና ስም ለእኛም ለሚመጣውም ትውልድ ባጠቃላይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ብርሀናዊ ነገ ስንል አባይን ገድበን የከሰርንውን ትላንትና በልማትና በብልጽግና መመለስ አለብን እላለሁ። ይሄ የሁላችሁም ሃሳበን እንደሚሆን አልጠራጠርም። ምክንያቱም ድህነት መሮናል፣ ማጣት በቃን ብለን የተነሳንበት ጊዜ ስለሆነም ነው። የዛሬ ሰው ናችሁ..ለሀገራችሁ አስፈላጊ የምትሆኑት ዛሬ ነው። ለሀገርም ሆነ ለትውልድ ብርሃን የምትሆኑበት ጊዜ ላይ ናችሁ..ብርሃናችሁን አብሩ። ዓደዋ በአባቶቻችን አንድነት የተጻፈ የእያንዳንዳችን ታሪክ ነው። ዓድዋ ህብረት የወለደው የኢትዮጵያዊያን የክብር ጥግ ነው። እኛም ከሁለተኛው ዓድዋ ጋር ግብ ግብ ውስጥ ነን። ሁለተኛውን ዓደዋ በድል ልናጠናቅቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። እናንተ ብኩራን..እናንተ ጸዐዳ መልኮች..እናንተ ኢትዮጵያዊ ክንዶች..እናንተ ብርሃናማ ትውልዶች በዚህ ዘመን ላይ የአባይ ፋና ወጊ ሆናችሁ በመቆማችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች።

አባይ ውሃ እንዳይመስላችሁ። አባይ ግድብ እንዳይመስላችሁ። አባይ ደማችን ነው። የሰማኒያ ብሄር ብሄረሰብ ቀለም ነው። አባይ ከግድብነት ባለፈ የአንድነታችን ካርታ ነው። ሁለተኛ ሀገራችን ነው። ለአባይ አንድ ብር ስታዋጡ ነገ ለሚፈጠሩት ልጆቻችሁ ቤት እየሠራችሁላቸው እንደሆነ ልብ ልትሉ ይገባል። ለአባይ ግድብ ቦንድ ስትገዙ ከድህነት እየወጣችሁና ወደሚደነቅ ብርሃናዊ ነገ እየተሸጋገራችሁ እንደሆነ ይሄንንም አትርሱ። ግድባችንን ለማደናቀፍ አሁን ላይ ከግብፅና ሱዳን እኩል አሜሪካና ሌሎች ሀገራትም ተነስተውብናል። እኛ ግን በአንድነት እንደጀመርንው ሁሉ በአንድነት በመቆም መጨረስ ይኖርብናል። ከተለያየን ኃይል አይኖረንም። በታሪክ ውስጥ የሠራናቸው ገድሎች ሁሉ በተባበረ ክንድ ያመጣናቸው ናቸው።

አሁንም በአባይም ሆነ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት በመቆም የጠላትን ኃይል ድል መንሳት ይቻለናል። የአባቶቻችንን አደራ እንፈጽም ዘንድ በአንድነት መቆም አማራጭ የሌለው ነገር ነው። በአባይ ትውልድ ላይ ተፈጥረን ወደ ኋላ የለም። የዘመናት ቁጭታችንን የምንወጣበት ጊዜ ላይ ነን። በዚህ ትውልድ ላይ ተፈጥሮ ለሀገሩ ጥሩ ነገር አለመሥራት ማለት ሀገር ከመክዳት ጋር አንድ ነው። በዚህ ትውልድ መካከል ቆሞ ለህዝብ አለመድከም ማለት አደራ በልነት ነው። እያንዳንዳችን ለሀገር የሚሆን ኃይል አለን። እንደ ሙሴ ሀገር አሻጋሪ እንጂ ሀገር ከጂ መሆን ራስን በታሪክ ድርሳን ላይ ማቆሸሽ ነው። ተወልደን ያደግንው፣ የተማርንው፣ ወልደን የከበድንው በአጠቃላይ ለቁም ነገር የበቃንው በዚህ ሀገርና በዚህ ህዝብ ውስጥ ነው። ይሄ ህዝብ ደግሞ ከእኛ ሌላ ማንም የለውም። ሀገር ተስፋዋን የጣለችው በእኛ ላይ ነን። ትውልድ ይመጣል ትውልድ ይሄዳል።

በታሪክ ውስጥ ስንዘከር ለመኖር በጊዜአችን ጠቃሚ ነገር እንሥራ። መልካም ነገ የሚፈጠረው በመልካም ዛሬ ነው። አዲሱ ትውልድ የሚፈጠረው ዛሬ ላይ ባለንው በእኛ አሻራ ነው። አሻራዎቻችን የነገ መልኮቻችን ናቸውና ለምናደርገው ለማንኛውም ነገር ጥንቃቄ ያሻናል። ለራሳችን ኖረን የምናተርፈው አንዳች ነገር የለም። ሀገር የምትበለጽገው በእኔና በእናንተ አስተዋጽኦ ልክ ነው። ተምረን ውጭ ሀገር የምንሄድ ከሆነ፣ ጥሩ ነገር ስናገኝ ዜግነት የምንቀይር ከሆነ ውለታ በል ነው የምንሆነው። ሀገራችን ላትመቸን ትችላለች፣ ፖለቲካውን ላንወደው እንችል ይሆናል ደስ የማይሉ ብዙ ነገሮችን እያየን ይሆናል ይሄ ሁሉ የሚስተካከለው ግን ሀገር ጥሎ በመሰደድ ሳይሆን ችግሮቻችንን ለመፍታት ለንግግር ስንቀመጥ ነው። ለጋራ ክብር በጋራ መሥራት ስንችል ነው።

እንደ ሀገር በርካታ ችግሮች አሉብን ችግሮቻችን የሚፈቱት ደግሞ በእኛው እንጂ በአሜሪካና በአውሮፓ ኃይል አይደለም። ስልጣኔ የራስን መሰረት መገንባት ነው። መሰረታችን ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። መሰረታችን ደግሞ ድሀ ህዝብ ነው። ብዙ ነን እኮ እንደብዛታችን ለሀገር ግንባታ የበኩላችንን ማድረግ ብንችል አይደለም አባይን ቀርቶ ሌላም ተዐምር መሥራት እንችላለን። የነገ መጻኢ ዕድላችንን በዛሬአችን መወሰን አለብን። በእኛ ዛሬ የሌሎችን ብሩህ ነገ እንሥራ። በእኛ ዘመን የልጆቻችንን መጪ ጊዜ አዲስ እናድርግ። አባይን ለመገንባት ምን ያክል ዋጋ እንደከፈልን ሁላችሁም የምታውቁት ሀቅ ነው። በዚህ የአስር ዓመት ድካማችን ውስጥ ብዙ አንድነትና ብዙ ትብብሮችን አይተናል። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ ምንም መሥራት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየንበት ጊዜ ላይ ነን።

ከፊታችን ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀው ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ይካሄዳል ይሄ ደግሞ ስንጠብቀው የነበረ ሌላው ደስታችን ነው። አባይ ነፍስ ዘርቶ ብርሃን ሊሆነን ዳዴ ላይ ነው። አባይ ከወቀሳና ከእርግማን ወጥቶ የትውልድ ተስፋ ሊሆን ከጫፍ ደርሷል። ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ጊዜ ለእኛ መልካም ነው። በአባይ የትንሳኤ ብስራት ሠርግና ድላችን ከፊት ነው። ድካማችን ፍሬ ሊያፈራ አበባ ላይ ነው። ይሄን ላደረገ ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ይገበዋል። በአባይ ትውልድ ላይ በመፈጠራችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል። እናተ የዚያኛውም ሆነ የዚህኛው ትውልድ ደማቅ ቀለሞች ናችሁ። መቼም የማደበዝዙ..መቼም የማጠይሙ ኢትዮጵያዊ ሀቅ። አበቃው። ቸር ሰንብቱ።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 .